በአፍሪካ ምድር የተወለደ፣ ያደገና የተማረ አንድ ሰው አለ፡፡ ጠላትን መበቀል እንደ ጀግንነት በሚታይበት አህጉር የተወለደና ያደገ ሰው ነው፡፡ በሰው ልጆች መካከል በቆዳ ቀለም ምክንያት አድልዎ መደረግ እንደሌለበት በማመንና ለሰዎች እኩልነትና ነፃነት በመታገሉ ምክንያት መልካም ከሆነው የጎልማሳነት ዕድሜው 27 ዓመትን በእስር ቤት አሳለፈ፡፡
ከብዙ ትግልና ጽናት በኋላ ከእስር ቤት ተፈታ፡፡ ከእስር ቤት ከወጣ ከአራት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በነፃ ምርጫ ላይ ተሳተፈ፡፡ በምርጫው በማሸነፍ የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያ የጥቁር ፕሬዘዳንት ለመሆን በቃ፡፡ እርሱን በእስር ቤት እንዲማቅቅ ባደረጉ ሰዎች ላይ መፍረድ የሚያስችል ሥልጣንን አገኘ፡፡ ሆኖም ፕሬዘዳንት ኒልሰን ማንዴላ በጠላቶቹ ላይ የሥልጣን በትሩን ከማሳረፍ ይልቅ ለእነርሱ ይቅርታ ማድረግን መረጠ፡፡ የዘር ጥላቻና አድልዎ በተንሰራፋበት ሀገር ውስጥ በዜጎች መካከል ሰላም፣ እርቅና ይቅርታ እንዲደረግ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ምሕረትና ይቅርታ በጥላቻ ላይ እንዲነግስ አደረገ፡፡
ኒልሰን ማንዴላ በግፍ ያሰሩትንና ብዙ ሥራ መሥራት የሚችልበትን የሕይወቱን ወርቃማ ዘመን በእስር ቤት እንዲያሳልፍ ያደረጉትን ጠላቶቹን ፍርድ ቤት ማቆምና እነርሱም እርሱ ወደነበረበት እስር ቤት እንዲወርዱ ማድረግ መብቱና ሥልጣኑ ነበረው፡፡ ሆኖም ‹‹ዐይን ለዐይን፣ ጥርስ ለጥርስ›› የሚለውን መርህ ከመጠቀም ይልቅ ክፉ ነገር ላደረጉ ጠላቶቹ መልካም ነገር ለማድረግ ወሰነ፡፡ ፍትሕን ብቻ ተከትሎ ፍርድ ከመስጠት ይልቅ በምሕረት የሚገኘው ውጤት ለራሱና ለሀገሩ ዘላቂ ውጤት እንዳለው ተገነዘበ፡፡ ትክክለኛ ነገር የሆነውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛና እጅግ መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ራሱን አዘጋጀ፡፡
በዚህ ዓለም ከተነሱ የሀገር መሪዎች መካከል ተወዳዳሪ የሌለውን ታሪክ የሠራ፣ በዓለም ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ አክብሮት የተጎናጸፈ ብቸኛው የሀገር መሪ ነው፡፡ ለዚህ አክብሮት ዋና ምክንያት የሆነው ኒልሰን ማንዴል ይቅርታ ማድረጉና ይቅርታ እንዲሰፍን ሁኔታን በማመቻቸቱ ነው፡፡ ዛሬ ኒልሰን ማንዴላ የነጻነት፣ የዲሞክራሲና የይቅርታ ተምሳሌት ነው፡፡ ከኒልሰን ማንዴላ አመለካከትና ድርጊት ይቅርታ ማድረግ ለአድራጊው ክብርን፣ በሰዎች መካከል ሰላምን፣ ለሀገር ብልጽግናን እንደሚያመጣ እንማራለን፡፡
ኒልሰን ማንዴላ ለጠላቶቹ ምሕረት ማድረግን ከማን ተማረ? እኔ ለዚህ ጥያቄ መልስ አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር አውቃለሁ፡፡ ለጠላቶች ይቅርታ ማድረግን ያስተማረን አንድ ሐዋርያ ነበር፡፡ እርሱም ኢየሱስ ነው፡፡ በሰው ሥርዓት መሠረት የፍርድ ቤት ሂደት ሁሉ ከተሟላ በኋላ ነበር ኢየሱስ ወደ ስቅለት የተወሰደው፡፡ በኢየሱስ ላይ ክስ ቀርቦበት ነበር፡፡ ከሳቹ ነበሩ፡፡ በደንቡ መሠረት ከሳሾቹ ምስክር አምጥተው በኢየሱስ ላይ አስመስክረውበታል፡፡ በወቅቱ የነበረውም ዳኛ በሥርዓቱ መሠረት የኢየሱስ መከላከያ ተቀባይነት ባለማግኘቱ በስቅላት እንዲሞት ፈረደበት፡፡ ስለዚህ በሰዎች እይታ ኢየሱስ ሞት የሚገባው ወንጀለኛ ነበር፡፡
በዘመኑ የነበሩ ወታደሮች ደግሞ ይህን ፍርድ የማስፈጸም ግዴታ ስለነበረባቸው ኢየሱስን ገርፈው መስቀል አሸክመውት ወደ ሚሰቀልበት ጎልጎታ ሥፍራ ወሰዱት፡፡ ከዚያም በመስቀል ላይ ሰቀሉት፡፡ የእርሱ የእጅ ሥራዎች የሆኑ ሰዎች በእርሱ ላይ እንዲህ ያለ ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ሲፈጽሙ ሲመለከት ኢየሱስ አዘነላቸው፡፡
ኢየሱስ ከሰማይ ወደ ምድር እንዲመጣ ያደረገው ዋናው ጉዳይ የሰዎች በደል የሚወገድበትን መንገድ መክፈት ነው፡፡ ሰዎች በመስቀል ላይ ቢያሰቃዩትም የመጣበትን ዓላማ አልረሳም፡፡ እርሱም ለሰው ልጆች የኀጢአት ይቅርታን ማስገኘት ነው፡፡ የመስቀል መከራ ተልዕኮውን አላስረሳውም፡፡ የእኛ ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያሰቃዩት ሰዎች ይቅርታ እንዲደረግላቸው አባቱን ለምኗል፡፡ ለበደሉን ሰዎች ይቅርታ ከማድረግ አንፃር ምን ያህል ክርስቶስን ተከትለናል?
ኢየሱስ ለእነዚህ ክፉ አድራጊዎች ይቅርታ እንዲደረግ ያቀረበው ምክንያት ነበር፡፡ ይኸውም እነዚህ ሰዎች ‹‹ የሚያደርጉትን አያውቁም›› የሚል ነበር፡፡ በእርግጥ ሰዎቹ በኢየሱስ ላይ ግፍ የተሞላበት መከራ ሲያደርሱበት የሚያደርጉትን ነገር አያውቁም ማለት ይቻላል?
በኢየሱስ ላይ ክፉ ድርጊቶችን የፈጸሙ ሰዎች ሕግን ባለማወቅ እንዲህ ያለውን ወንጀል መፈጸማቸው ከተጠያቂነት ያድናቸዋልን? በሕግ ‹‹ሕግን አለማወቅ ከወንጀል ነፃ አያደርግም›› ይባላል፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንዲሰቀልና መከራ እንዲቀበል ከዚያም እንዲሞት ያደረጉ ሰዎች ግን የሚያደርጉትን ነገር የማያውቁ አልነበረም፡፡ ኢየሱስ ከዚህ ምድር እንዲወገድ፣ በሕይወት እንዳይኖር ከመፈለጋቸው የተነሣ ነገር ፈልገውበት፣ የሐሰት ምስክርነት በማቆም ነበር እንዲሰቀል ያደረጉት፡፡ ስለዚህ ሆን ተብሎ ታስቦበትና ታቅዶበት፣ ምቹ ሁኔታ ተመቻችቶ እንዲያዝና እንዲሰቀል አደረጉ፡፡ ይህ ማለት እነርሱ ነገር ባይፈልጉበትና በሐሰት ምስክርነት ባይዙት ኖሮ ኢየሱስ የመስቀል ሞት የሚገባው ወንጀለኛ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ኢየሱስ ንጹሕ ሰው እንደሆነ ያውቁታል፡፡
ኢየሱስ ለመስቀል ሞት አልፎ እንዲሰጥ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠው ጲላጦስ ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በማድረግ ‹‹ባቀረባችሁበት ክስ አንዳች ወንጀል አላገኘሁበትም›› (ሉቃ23፡14) በማለት በአደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ተናግሯል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከዚያ ቀደም ብሎ ተመሳሳይ ምርመራ ያደረገውም ሄሮድስ ምንም በደል አላገኘበትም (ሉቃ23፡15)፡፡ ስለዚህ ጲላጦስ ለሞት የሚያበቃው ምንም ወንጀል እንዳልሠራ በመግለጽ ለሕዝቡ እርካታ ብቻ በመግረፍ ለመፍታት ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ሕዝቡ ግን በአንድ ድምፅ ኢየሱስን ‹‹ስቀለው! ስቀለው›› አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሡ ኢየሱስ ለሞት የሚያበቃው ወንጀል እንዳልሠራ እያወቀ በመንግሥቱ ላይ ሕዝቡ ዐመጽ እንዳያስነሳ በመፍራት ኢየሱስን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡
ስለዚህ በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንዲሞት ያደረጉና በመስቀል ላይ ያሰቃዩት ሰዎች የሚያደርጉትን ነገር አያውቁም ማለት እንዴት ይቻላል? ወንጀል ያልሠራውን ሰው ወንጀለኛ እንደሆነ አድርገው ሰቀሉት፡፡ ስለዚህ ሆን ተብሎ የተሠራ ግፍና ተንኮል ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስም ከዚያ በፊት ሲያስተምር በነበረበት ወቅት ‹‹መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የላቸውም›› (ዮሐ15፡22) በማለት በእርሱ መምጣት ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ በመደረጉ ባለማመናቸው ተጠያቂዎች እንደሚሆኑ ተናግሯል፡፡
የታሪክ ክስተቱ እንዲህ ሆኖ ሳለ ኢየሱስ ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁም›› ማለቱ ምን ለማለት ነው? ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ እነርሱ የሚያደርጉትን ነገር እያወቁ አይደለም ማለቱ ሳይሆን ይህ ክፉ ሥራ በማን ላይ እያደረጉ እንደሆነ በትክክል እንዳልገባቸው ለማሳየት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ እንዲህ ዐይነት ወንጀል በመፈጸማቸው በእነርሱና በልጆቻቸው ላይ ሊመጣ ያለውን ፍርድ አለማስተዋላቸውን ለመግለጽ ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ በትክክል ማን እንደሆነ አልተገነዘቡም ነበር፡፡ ኢየሱስ የክብር ጌታ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ፣ መሲሕ እንደሆነ ቢገነዘቡ ኖሮ በመስቀል ላይ አይሰቅሉትም ነበር፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‹‹አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ እናንተ ይህን ያደረጋችሁት እንደ አለቆቻችሁ ሁሉ ባለማወቅ እንደሆነ ዐውቃለሁ›› (የሐሥ3፡17) በማለት ሕዝቡና መሪዎቻቸው ባለማወቅ ኢየሱስን እንደ ሰቀሉ ተናግሯል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ‹‹ከዚህ ዓለም ገዦች አንዳቸውም ይህን ጥበብ አልተረዱትም፤ ቢረዱትማ ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር›› (1ቆሮ2፡8) በማለት ኢየሱስን የሰቀሉት ሰዎች እርሱን በትክክል አለመረዳታቸውን ይገልጻል፡፡ እነዚህ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ ማንነት ግንዛቤ እንዲያገኙ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ኢየሱስ ማንነቱን በቃልና በተግባር ገልጾላቸዋል፡፡ ነገር ግን ለመቀበልና ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ሆኖም ኢየሱስ ያንን ሁሉ ነገር አልቆጠረባቸውም፡፡ ለሰዎቹ ራራላቸው፡፡ በእነርሱ ላይ መቆጣትና መፍረድ ሲገባው፤ ግን ምሕረትን አሳያቸው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ የክብር ጌታ እንደሆነ ቢገባቸው ኖሮ እንደማይሰቅሉት ሲናገር ምናልባት የራሱንም ታሪክ ሳያስብ አይቀርም፡፡ እርሱ ራሱ ክርስቶስን የሚያሳድድ ሰው እንደነበር ተነግሮለታል፡፡ የኢየሱስን ደቀመዛሙርት ለማሠር፣ ለመግደልና እምነቱንም ለማጥፋት የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጦ የተነሣ ለሃይማኖቱ ቀናተኛ የሆነ ሰው ነበር፡፡ ሆኖም ኢየሱስ ከተገናኘውና ታሪኩ ከተለወጠ በኋላ ዞር ብሎ ያሳለፈውን ታሪኩን ሲመለከተው ‹‹ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረት ተደርጎልኛል›› (1ጢሞ1፡13) በማለት ይገልጻል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰሙና በእርሱ ስም የሚደረጉትን ድንቅና ተዓምራትን ስላዩ ብቻ አይረዱም፣ አያምኑምም፡፡ ሰዎች እያዩ እንዳያስተውሉና እንዳያምኑ አእምሮአቸውን የቆለፈ የሆነ ነገር እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን ማወቅና ማመን የግል ሰብዓዊ ድርሻ ቢኖርበትም የእግዚአብሔር ዕርዳታ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የሰውን አእምሮ/ መንፈስ ሲያበራ፣ ሰዎች የጠሉትን መውደድ፣ የሚያሳድዱትን መፈለግ፣ የሚቃወሙትን ማገልገል ይጀምራሉ፡፡ በደማስቆ መንገድ ላይ ለአሳዳጁ ሳኦል የበራለት ብርሃን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን እምነት ለሚቃወሙ ሰዎች ሁሉ ሊበራላቸው ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ እኔ ክርስቶስን በማመን በዘገዩትና እምቢ ብለው በሚቃወሙ ሰዎች ላይ ከመፍረድና ከመኮነን ይልቅ እግዚአብሔር ለእነርሱ ምሕረት እንዲያደርግላቸውና አእምሮአቸውን አብርቶላቸው በክርስቶስ የሚገኘውን መልካም ሕይወት ማየት እንዲችሉ እንዲያደርግ መጸለይ የተሻለ መንገድ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ኢየሱስ ለሰዎች በደል ይቅርታ ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር እንደሆነ በማመኑ ነበር ወደ አባቱ ‹‹ይቅር በላቸው›› ብሎ የለመነው፡፡ በዚህ ልመና ኢየሱስ በክፉ አድራጊዎቹና በእግዚአብሔር አብ መካከል የአማላጅነትን ሥራ እንደ ሠራ እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁም›› የተባሉ ሰዎች እርሱ በመስቀል ላይ እንዲሞት ዋና ተዋናይ የነበሩና ተባባሪዎቻቸው እንዲሁም በፍርዱ መሠረት በመስቀል ላይ በመስቀል የሞት ቅጣቱን የሚያስፈጽሙ ወታደሮችንም የሚጠቃልል ሐሳብ ነው፡፡ ክፉ አድራጊዎቹንና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ ልመና አቀረበ፡፡ ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች እያደረጉት ባሉት ክፉ ድርጊት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተገቢውን ፍርድ እንደሚያገኙ ያውቃል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ምሕረት እንዲያደርግላቸው ጣልቃ ገብቶ ለመነላቸው፡፡
ኢየሱስ የመጣበት ዋና ተልዕኮው ለኀጢአተኞች ይቅርታ እንዲሆን ነው፡፡ በመስቀል ላይ የመከራ ጽዋ እየጠጣ ሳለ እግዚአብሔር ለክፉ አድራጊዎቹ ምሕረት እንዲያደርግ በመለመኑ በብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለ እርሱ የተነገረውን ‹‹ስለ ዐመጸኞችም ማለደ›› (ኢሳ53፡12) የሚለው የትንቢት ቃል ፈጸመ፡፡
ብዙዎቻችን እኛ ምንም ክፉ ነገር ሳናደርግ ሰዎች በእኛ ላይ የሐሰት ምስክርነት አስመስክረው አስፈርደውብን ማረሚያ ቤት እንድንገባ ወይም የገንዘብ ቅጣት እንድንቀጣ ቢያደርጉ የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወርዳ እንድትበላቸው እንጂ እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው እንለምናለን ብዬ አልገምትም፡፡ እግዚአብሔር እነዚያ ሰዎች ሐሰተኞች፤ እኛ ግን እውነተኞችና ንፁሓን እንደሆንን በአደባባይ በተዓምር ምልክት እንዲሰጥ እንለምናለን፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ልዩ ተዓምር ፈጥሮ ፍትሕን በአደባባይ የሚያሳይበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ እኛ ምሕረትን ለምነንም እግዚአብሔር ግን እነዚያን ክፉ አድራጊዎችን ሊበቀል ይችላል፡፡ ያ የእኛ ድርሻ ሳይሆን የመለኮት ኃላፊነት ነው፡፡ እኛ እንድናደርግ ምሳሌ የተተወልን ሰዎች በእኛ ላይ ክፉ ነገር ሲያደርጉ እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው መለመን ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ማለት በሕይወታችን የእርሱን ፈለግ መከተላችን ነው፡፡ ኢየሱስ ሰዎች በእርሱ ላይ ክፉ ነገር ሲያደርጉ ያውም ለሞት አሳልፎ ሲሰጡት ምሕረትን ከለመነላቸው ከእኛም ተመሳሳይ ነገር እንደሚጠበቅብን ማሰብ አለብን፡፡ በእኛ ላይ ክፉ ነገር ለማድረግ ለሚተጉ ሁሉ እግዚአብሔር በምሕረቱ እንዲያስባቸው የመጸለይ ጥሪ አለን፡፡ ይህ የክርስቶስ ተከታዮች መርህ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በመሆን የኢየሱስን መንገድ መከተል የለም፡፡
ሰዎች ለክፉ ሥራ ተገቢውን አጸፋ መመለስ (መበቀል) ተቀባይነት እንዳለው ሥርዓት በተቀበሉበት ዐውድ፤ ለሰዎች ክፉ ድርጊት ምሕረት ማድረግ እንደ ጅልነት ይታያል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ግን ከዚህ የሕይወት ደረጃ በላይ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ ሰብዓዊነት ከሌሎቹ የተሻለ በመሆኑ ሳይሆን እነርሱ ለመከተል ምርጫ ያደረጉት ኢየሱስ እንዲህ ዐይነት ሕይወት በመኖሩ ፈለጉን እንዲከተሉ በማሳየታቸው ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በእርሱ ላይ ክፉ ሲያደርጉ የነበሩትን ሰዎች ይቅር በማለቱ ተዓምር ያደረገ ሊመስለን ይችላል፡፡ ኢየሱስ ያደረገው ትልቁ ነገር በሰላም ጊዜ ተከታዮቹን ያስተማረውን ትምህርት በመስቀል ላይ መከራ ሲደርስበት በሕይወቱ በተግባር ላይ አዋለው፡፡
ኢየሱስ እንዲህ በማለት አስተምሮ ነበር፡-
‹‹እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ›› (ማቴ5፡44)
‹‹ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚበድሏችሁም ጸልዩ›› (ሉቃ6፡27-28)
ኢየሱስ መከራና ችግር ሲመጣበት ያስተማረውን በመኖር አሳየ እንጂ ‹‹እኔ ለእናንተ አስተማርኩኝ እንጂ እኔን አይመለከተኝም›› አላለም፡፡ የመስቀል ስቃዩን ያስተማረውን በሕይወት ተርጉሞ ለማሳየት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቀመበት፡፡ ኢየሱስ ያስተማረውን ትምህርት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በመኖር የሚያሳይ የመንፈሳዊ አገልጋይ አርዓያ ነው፡፡
ክርስቶስ ኢየሱስን በእውነት የተከተሉ ሰዎችም በዘመናቸው የእርሱን ፈለግ በመከተል መከራና ስቃይ ያደርሱባቸው የነበሩትን ሰዎች ይቅር ብለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል እስጢፋኖስ አንዱ ነበር፡፡ እስጢፋኖስ ስለ ኢየሱስ በአደባባይ በመመስከሩ ምክንያት ሰዎች በቁጣ ተሞልተው በድንጋይ ወግረው ገደሉት፡፡ እስጢፋኖስ የድንጋይ ናዳ ሲወርድበት የወሰደው እርምጃ ተንበርክኮ ወደ ሕያው እግዚአብሔር በታላቅ ድምጽ ‹‹ጌታ ሆይ፤ ይህን ኀጢአት አትቁጠርባቸው›› በማለት ጸለየ (የሐሥ7፡60)፡፡ ኢየሱስን እንኳ እርሱ አምላክ-ሰው ስለሆነ የበደሉትን ሰዎች ይቅር ለማለት ቻለ ብንል እስጢፋኖስ ግን እንደ ማንኛችንም ሰው ነበር፡፡
የክርስቶስ ሐዋርያት በዘመናቸው ኖረውበት ለክርስቶስ ተከታዮችም ያስተላለፉት መልዕክት ለበዳዮቻችን ይቅርታ ማድረግን ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱ የሕይወት ልምምድ ‹‹ሲረግሙን እንመርቃለን፣ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ ስማችንን ሲያጠፉ መልካም እንመልሳለን›› (1ቆሮ4፡12) በማለት ተቃዋሚዎችን እንዴት እንዳስተናገዳቸው ይገልጻል፡፡ ከክርስቶስ ምሳሌነት እንዲሁም ከራሱ የሕይወት ልምምድ በመነሳት ሐዋርያው አማኞች ማድረግ የሚገባቸውን ነገር እንዲህ በማለት ይመክራቸዋል ‹‹የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትረግሙ›› (ሮሜ 12፡14)፡፡
ስለዚህ እንደ ክርስቶስ ተከታዮች እምነታችንን የሚቃወሙና የሚያሳድዱንን ሰዎች መርገም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ሳይሆን የክፉ መንፈስ ተልዕኮና ተግባር ነው፡፡ ወንጌል ያዘዘን ጠላቶቻችንን እንድንመርቅ እንጂ እንድንረግማቸው አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር የጸሎት ዘይቤአችንን መቃኘት አስፈላጊ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጸሎታችን ውስጥ የምጠቀምባቸው ቃሎች ከክርስቶስ ተከታይ አንደበት የሚወጡ አይመስሉም፡፡ ለእኛ መልካም የሚሆነውና የእግዚአብሔርም ሐሳብ ከሙላት የሚደርሰው አካሄዳችን እንደ እግዚአብሔር ቃል ሲሆን ነው፡፡ በጸሎታችንና በስብከታችን ጊዜ የምንጠቀምባቸው መጥፎ የሆኑ ቃላት የእምነታችንን ተቃዋሚዎች ከመጉዳት ይልቅ በእኛው ላይ መዘዝ ይዘው ይመጣሉ፡፡ እኛን ያረክሱናል፡፡ ከአንደበታችን የሚወጡ መጥፎ ቃላት ስለ እኛ አስተሳሰብና አመለካከት መጥፎነት የሚናገሩ መልዕክተኞች ናቸው፡፡ መጥፎ ቃላት በመናገር የሚመጣብን ስደት ደግሞ እኛው በራሳችን ላይ ያመጣነው እንጂ በክርስቶስ ስም የምንቀበለው ስደት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ራሳችንን ማንጻት ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
በክርስቶስም ሆነ በሐዋርያት ሕይወት መስቀሉ፣ መከራውና ስቃዩ የመጣው በእነርሱ ጥፋት አልነበረም፡፡ በኢየሱስ ላይ ማንም በመስቀል ላይ እንዲሞት የሚያደርግ ጥፋት አላገኘበትም፡፡ የሐሰት ክስ ግን ተመስርቶበታል፡፡ ሐዋርያትም ያጠፉት ጥፋት አልነበረም፡፡ የስደቱና የመከራው መንስኤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም በቆራጥነት መነሳታቸው ነው፡፡ የሰዎችን ንብረት አልቀሙም፣ ሰዎችን አልተሳደቡም፣ ሰዎችን አልከሰሱም፣ ምንም ወንጀል አልሰሩም፡፡ እንደ ትልቅ ወንጀልና ጥፋት ሆኖ የተቆጠረባቸው የክርስቶስን ወንጌል መስበካቸው ነው፡፡
በራሳችን ስህተትና ጥፋት ስደት እንድነሳብን አድርገን መከራ ብንቀበል እኛው ልንወጣው ይገባናል፡፡ እንዲህ ዐይነቱ መከራ የእግዚአብሔርን መንገድ በመከተል ከሚመጣው መከራ የተለየ ነው፡፡ ስለ ራሳችን የምንሰደደው ስደት እንጂ በክርስቶስ ስም የምንሰደደው ስደት አይደለም፡፡ የክርስቶስ ሐዋርያት ይህን ለይተው አስተምረዋል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ
‹‹ክፉ ሥራ ሠርታችሁ መከራ ብትቀጡና ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል; ነገር ግን መልካም ሥራ ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉና ብትታገሡ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል›› (1ጴጥ2፡20) ይላል፡፡
ሐዋርያው ጴጥሮስ ለዚህ ምክሩ እንደ ምሳሌ የተጠቀመው ኢየሱስ መከራ ሲቀበል መከራ ያደረሰቡትን ሰዎች ያስተናገደበት ሁኔታ ነው፡፡
‹‹ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው፡፡ እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኮል አተገኘበትም፡፡ ሲሰዱቡትም መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ›› (1ጴጥ2፡21-23)
በዚህ ዘመን እኛ የክርስቶስ ተከታዮች ነን የምንል ወገኞች እየተቀበልን ያለው መከራና ስቃይ በራሳችን ጥፋት ወይስ በንጹሕ ልብና በተቀደሰ ሕይወት በመኖር ክርስቶስን በመከተላችንና እርሱ ባስተማረን መንገድ ሰዎችን ሁሉ የሚያድነውን የክርስቶስን ወንጌል በመስበካችን የመጣብን ነው? ይህን ለይተን ማወቁ አስፈላጊ ነው፡፡ የመጀመሪያውን እኛው ራሳችን በራሳችን ላይ የምናመጣው ስደትና መከራ ሲሆን ሁለተኛ ግን ክርስቶስን በመከተላችን የሚመጣብን ነው፡፡ ለመጀመሪያው መንስኤው የእኛ ጥፋት ሲሆን ለሁለተኛ ግን እንደ ጥፋት የሚቆጠረው ክርስቶስን መከተልና እርሱን ማገልገል ነው፡፡
መልካም ነገር እያደረግን በክፉ ሰዎች መከራና ስቃይ ስደርስብን በትዕግስት መቻል ከክርስቶስ ተከታዮች የሚጠበቅ የሕይወት ሥነምግባር ነው፡፡ ‹‹ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው›› (1ጴጥ3፡9)፡፡
በሀገራችን በወንጌል ስብከትና በመዝሙራት የእግዚአብሔርን በረከት ስለ መውረስ ብዙ ይደመጣል፡፡ በረከትና መውረስ የሚሉ ቃላት በተደጋጋሚ ይነገራሉ፡፡ በረከትን መውረስ እንደ ግብ ቢቀመጥም፣ ሁሉም ስለተመኘ አያገኝም፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያስቀመጠውን በረከት መውረስ የሚቻለው እርሱ በሚያዘው መሠረት በመኖርና እርሱ ያዘዘውን ነገር በማድረግ ነው፡፡ በአቋራጭ ወደ በረከት የሚያደርስ መንገድ የለም፡፡ እንዲህ ዐይነት መንገድ ቢኖር ኖሮ ሰዎች ሁሉ ያንን መንገድ ፍለጋ ይሄዱ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደ አቋራጭ መንገድ የሚታዩ መንገዶች ደግሞ ከሥነምግባር የጎደሉ መንገዶች ናቸው፡፡
ስለዚህ የሚፈለገው በረከት እንዲወረስ ከተፈለገ የሥነምግባር ሕይወታችንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ በተለይ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ጽድቅ የተሞላበት ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንድናደርገው የመከረን መንገድ ሰዎች ክፉ ነገር ሲያደርጉብን ክፉ መመለስን መተው፣ ሰዎች ሲሰድቡን መልሰን መሳደብን መተውና እነርሱ ክፉ ነገር ሲያደርጉብን እኛ ደግሞ እንድንባርካቸው ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ያለብን ደግሞ በረከቱን ለመውረስ ሳይሆን እንዲህ ማድረግ በክርስቶስ አምኖ እርሱን የመከተል የሕይወት ጥሪ በመሆኑ ነው፡፡ በክርስቶስ ያመነን ስንባል እንዲህ ሆነን መኖር ስለሚገባን ነው፡፡ በዚህ ዐይነት የሕይወት ሥነምግባር ስንኖር በእግዚአብሔር የታቀደው በረከት ይመጣል፡፡ ካልሆነ የእግዚአብሔር በረከት ‹‹ባርከን...ባርከን...ባርከን›› እያሉ ቃላትን በመደጋገምና ‹‹ተባረኩ...ተባረኩ....ተባረኩ›› እያሉ በመጮኽና በፉከራ ብቻ አይመጣም፡፡ የተባረከ ሕይወት የይቅርታና የምሕረት ውጤት ነው፡፡





